serving the whole person

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ
ከፕሬዚዳንቱ የተላለፈ የ2012 ዓ.ም የመልካም ምኞት መልዕክት
አዲስ አበባ

በስመ አብ፣በወልድ፣በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ፤ አሜን!
• በጌታ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ መላው የሀገራችን ህዝቦች ፤
• ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ-ኢትዮጵያውን፤
• በየሆስፒታሉና በየማረሚያው ቤት የምትገኙ ዜጎች፤
• እና ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ

ከሁሉ አስቀድሜ በምህረቱና በቸርነቱ ሁላችንንም በሰላምና በጤና ጠብቆ ለ2012 ዓ.ም. ላደረሰን ለኃያሉ አምላካችን ክብርና ምስጋና ይድረሰው እያልኩ ለዚህ አዲስ ዓመት ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ በማለት በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና በራሴ ስም መልካም ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከጥፋቱ ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅ አዲስ ቃል ኪዳን ሲገባለት እንግዲህ “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም” (ዘፍ. 8፡22) አለው፡፡

ከዚህ እውነታ የምንረዳው የበልግ እና የመከር፣ የበጋ እና የክረምት እንዲሁም የቀን እና የሌሊት ተፈጥሮአዊ ኡደቶች ሳይዛነፉ ወይም ሳይገቱ እየተለዋወጡ መቀጠላቸው ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ቃል ኪዳን የተነሳ መሆኑ ነው፤ እግዚእብሔርም ይህንን ቃል ኪዳኑን ሳያጥፍና የግዜ ኡዴቱም ሳይዛነፍ እኛ ኢትዮጵያን ዓመቱን በተለይም የክረምቱን ጊዜ በሰላም አጠናቅቀን ወደ አዲስ አመት በሠላም እንድንሸጋገር አድርጎናልና የዘመናት አምላክ የሆነውን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡

ግዜ መከሰቱና ማለፉ በራሱ ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፤ ግዜዎቹ እንዲሁ በከንቱ ሳይቋረጡ ለኡደት ብቻ የተፈጠሩ ሳይሆኑ የሰው ልጆች እንዲጠቀሙባቸው ፤ ለኑሮ የሚበጀውን እንዲከውኑባቸው ከእግዚአብሔር የተሰጡን ሥጦታዎች መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ጠብቆ በታማኝነት ግዜያትን ለጥቅማችን የሚያለዋውጣቸው ከሆነ እኛም እንዲሁ በጸጋው በአደራ ለተሰጠን የግዜ ሥጦታ ታማኝ ባለአደራዎች በመሆን ለበጎ ተግባር ብቻ ልንጠቀምባቸው ይገባናል፡፡

እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ሕዝብ ባለፈው ዓመት ያከናወናቸውን መልካም ተግባራት ሁሉ አጠናክረን በመቀጠልና በማጎልበት በሌላ በኩል ደግሞ ያልጠቀሙንንና የጎዱንን ነገሮች በማራገፍ የአዲሱን ዓመት አዲስ ምዕራፍ መጀመር የጠበቅብናል፡፡ በተለይም እንደ አገር በህዝቦቻችን መካከል፤ በብሔር፤ በቋንቋ እና በሃይማኖት ረገድ ያሉትን ልዩነቶች እንደ ጸጋ በመቀበል፤ የመቻቻልንም መንፈስ በማጎልበት እንደ አንድ አገር ህዝብ አብሮ ለመኖር ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ በብርቱ መትጋት ከዜጎች ሁሉ እንደሚጠበቅ ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት አገራችን ስታስተናግዳቸው ከነበረው የአለመግባባትና የግጭት ሁኔታዎች ተላቅቆ የሰላምና የፍቅር ኑሮን መምራት የሚቻለው እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ያለፈውን ሁሉ ለታሪክ ሸኝተናቸው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል አዲስ ታሪክ ለመሥራት ሁለም ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገው ትውልድ የሚሆን ስንቅ መሰነቅ የሚገባ እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ ተስፋ ሰጭ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖቻችን ወደየቄአቸውና ወደሰላማዊ ኑሮአቸው መመለሳቸው እጅጉን የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ከያንዳንዱ ዜጋ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ህዝቦቻችን ቸርነትን የኑሮአቸው መገለጫ ለማድረግ መትጋት ይገባቸዋል፤ ቸርነት የተደረገለት ወገን ለሌሎች ቸርነት በማድረግ መልካም ምላሽ መስጠት ሲገባው ተቃራኒ ውሳኔ ማድረግ፤ የማይገባ መንገድም መጓዝ ግን የማይገባ ነው፡፡

በዚህ አዲስ ዓመት ድህነትንና ሥራ አጥነትን ለመዋጋት የጋራ ጥረት ማድረግ፤ በቁርጠኝነትም መንቀሳቀስ ከህዝባችን የሚጠበቅ ነው፡፡ ድህነት በንግግር፤ በውይይት፤ ጥሩ የሚባሉትን እቅዶች በመንደፍ ብቻ አይወገድም፡፡ የድህነት መዲሃኒቱ ሥራ ብቻ ስለሆነ እርስበርስን በስራ በማትጋት ድህነትንና ስራ አጥነትን ለታሪክ ትቶ እስከማለፍ ጥረቶች በየደረጃው ሊደረጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡

ባለፈው ክረምት በንቃትና በመሰጠት መንፈሰ የተካሄደው የዛፍ ተከላ ዘመቻ እጅጉን ተስፋ ሰጭ ነበር፤ ህዝባችን ለአገራዊ አንድነት እንዲህ ቢተባበር ያገራችን ብልጽግና ሩቅ እንዳልሆነም ከዚሁ መገመት የሚቻል ነው፡፡ የአረንጓዴ ልማቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ሆኖ እስካሁን የተተከሉትን በመንከባከብ በመጪ ጊዜያትም ተመሳሳይ እንቅስቃሱ ለማድረግ የሚያበቁ ዝግጅቶችም ካሁኑ ሊታሰቡ እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

ይህ የጀመርነው አዲስ አመት በአገራችን በርካታ ፖለቲካዊ ተግባራት የሚከናወኑበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በተለይም ባገሪቱ ያሉት ፖለቲከኞችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገራችንና ለህዝቦቻችን ሰላምና ብልጽግና ሊተርፉ የሚችሉትን ፕሮግራሞቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ በማስተዋወቅ፤ በመልካም ስነ ምግባርና በሃላፊነት ስሜት አንዲንቀሳቀሱ ቤተ ክርስቲያናችን አደራ ትላለች፡፡

እግዚአብሔር የሰጠንን ይህን አገር በሁለም ዘርፍ ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ በማሸጋገር ያደገች፣የለማች፣የበለፀገችና ሕዝቦችዋም የሚኮሩባት ሃገር ለማድረግ በአንድነት እንድንነሳ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ እግዚአብሔር ሀገራችንንና ሕዝባችን እንዲባርክ ቤተ ክርስቲያናችን ቀጥላ በፀሎት የምትተጋ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም በዚህ በበዓል ወቅትም ሆነ በሌሎች ግዜያት ሁሉ በመካከላችሁ ያሉትን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በቸርነት እንድታስቧቸው እያሳሰብኩ አዲሱ ዓመት የሰላም የብልጽግና፤ የፍቅርና የመተሳሰብ ዓመት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡ በዓሉም የደስታ፤ የህብረትና የበረከት ጊዜ ይሁንላችሁ፤ ደግሜም እንኳን አደረሳችሁ ለማለት አወዳለሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አገራችንን ይባርክ፤ ይጠብቃት፤ ሰላሙንም ያብዛላት!

ቄስ ዮናስ ይገዙ
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት